1 Kings 17

ኤልያስን ቍራዎች መገቡት

1በዚህ ጊዜ ከገለዓድ ነዋሪዎች አንዱ የሆነው ቴስብያዊው ኤልያስ አክዓብን፣ “የማመልከው ሕያው እግዚአብሔርን፣ በእኔ ቃል ካልሆነ በቀር፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ዝናብ ወይም ጠል አይኖርም” አለው።

2ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ለኤልያስ መጣለት፤ 3“ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ባለው በኮራት ወንዝ ተሸሸግ። 4ውሃ ከወንዙ ትጠጣለህ፤ ቍራዎችም እዚያው እንዲመግቡህ አዝዣለሁ።”

5ስለዚህ እግዚአብሔር ያዘዘውን ፈጸመ፤ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ወዳለው ወደ ኮራት ወንዝ ሄዶ በዚያ ተቀመጠ። 6ቍራዎችም ጧትና ማታ እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ውሃም ከወንዙ ይጠጣ ነበር።

የሰራፕታዪቱ መበለት

7በምድሪቱ ላይ ዝናብ ባለመጣሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወንዙ ደረቀ። 8ከዚያም እንዲህ የሚል የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤልያስ መጣ፤ 9“ተነሥና ሲዶና ውስጥ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሄደህ ተቀመጥ፤ በዚያም አንዲት መበለት እንድትመግብህ አዝዣለሁ።” 10ስለዚህ ተነሥቶ ወደ ሰራፕታ ሄደ። ወደ ከተማዪቱ በር እንደ ደረሰም፣ አንዲት መበለት ጭራሮ ስትለቃቅም አገኛት፤ ጠርቶም፣ “የምጠጣው ውሃ በዕቃ ታመጪልኛለሽን?” ሲል ለመናት። 11ልታመጣለት ስትሄድ አሁንም ጠራትና፣ “እባክሽን፣ ቍራሽ እንጀራም ይዘሽልኝ ነይ” አላት።

12እርሷም መልሳ፣ “አምላክህን ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ዕፍኝ ዱቄትና በማሰሮ ካለው ጥቂት ዘይት በቀር ምንም የለኝም። እነሆ፤ ለራሴና ለልጄ ምግብ አዘጋጅቼ በልተን እንድንሞት ጭራሮ ለቃቅሜ ወደ ቤት ልወስድ ነው” አለችው።

13ኤልያስም መልሶ እንዲህ አላት፤ “አይዞሽ አትፍሪ፤ ወደ ቤት ገብተሽ እንዳልሽው አድርጊ፤ በመጀመሪያ ግን ከዚያችው ካለችሽ ትንሽ ዕንጐቻ ጋግረሽ አምጪልኝ፤ ከዚያም ለራስሽና ለልጅሽ ጋግሪ፤ 14የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እግዚአብሔር ለምድሪቱ ዝናብ እስከሚሰጥበት ዕለት ድረስ፤ ከማድጋው ዱቄት አይጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አያልቅም።’ ”

15እርሷም ሄዳ ኤልያስ እንደ ነገራት አደረገች፤ በዚህ ሁኔታም ኤልያስ፣ መበለቲቱና ቤተ ሰቧ ብዙ ቀን ተመገቡ፤ 16በኤልያስ በተነገረው የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ከማድጋው ዱቄት አልጠፋም፤ ከማሰሮውም ዘይት አላለቀም ነበርና።

17ከጥቂት ጊዜ በኋላም የባለቤቲቱ ልጅ ታመመ፤ ሕመሙ እየጠናበት ሄደ፣ በመጨረሻም ትንፋሹ ቀጥ አለ። 18እርሷም ኤልያስን፤ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፤ እኔ ምን አደረግሁህ? እዚህ የመጣኸው ኀጢአቴን አስታውሰህ ልጄን ለመግደል ነውን?” አለችው።

19ኤልያስም መልሶ፣ “ልጅሽን ስጪኝ” አላት፤ ልጁንም ከዕቅፏ ወስዶ እርሱ ወደሚኖርበት ሰገነት በማውጣት በዐልጋው ላይ አስተኛው። 20ከዚያም፣ “አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ ልጇን እንዲሞት በማድረግ ተቀብላ በምታስተናግደኝ በዚህች መበለት ላይም መከራ ታመጣባታለህን?” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 21በልጁም ላይ ሦስት ጊዜ ተዘርግቶ፣ “አምላኬ እግዚአብሔር ሆይ፤ የዚህ ልጅ ነፍስ ትመለስለት” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ።

22 እግዚአብሔርም የኤልያስን ጩኸት ሰማ፤ የልጁም ነፍስ ተመለሰችለት፤ እርሱም ዳነ። 23ከዚያም ኤልያስ ልጁን አስነሥቶ ከሰገነቱ ወደ ምድር ቤት አወረደው፤ ለእናቱም “ልጅሽ ይኸውልሽ፤ ድኖልሻል!” ብሎ ሰጣት።

24ከዚያም ሴቲቱ ኤልያስን፣ “አሁን የእግዚአብሔር ሰው መሆንህን፣ ከአንደበትህም የወጣው የእግዚአብሔር ቃል እውነት መሆኑን ዐወቅሁ” አለችው።

Copyright information for AmhNASV